ነባር ማህበረሰቦች በሰው ልጅ ህይወት ቀጣይነት ያላቸው አስተዋፅዖ
by IBC ~ November 1st, 2009. Filed under: CBD, ዓለም አቀፍ ስምምነት.ሞንቲርያል፣ 30 ኦክቶበር 2009 - ምንም እንኳን 6.3 ቢሊዮን ከሚሆነው የዓለም ህዝብ አነስተኛውን ቁጥር ቢይዙም፣ ነባር ማህበረሰቦች ከፍተኛውን የቋንቋና የባህል ተለያይነት የያዙ ሲሆን በነርሱ ሥር እየተጠበቁ ያሉት ባህላዊ ቦታዎችና የውሀ አካላትም ከፍተኛውን የብዝሀ ሕይወት ሀብት ይይዛሉ።
የነባር ማህበረሰቦችን እውቅት በመጠቀም የብዝሀ ሕይወት ሀብት እየተጠበቀ ከመሆኑም ባሻገር ሀብቱ በሂደት እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። ስለሆነም የማህበረሰቦችን እውቀት በመጠቀም የብዝሀ ሕይወት ሀብቱንና የዘረመል ተለያይነቱን በተሻለ ሁኔታ መንከባከብና መጠበቅ ይቻላል።
እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2፣ 2009 ከ300 በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ካናዳ (ሞንቲሪያል) በሚገኘው የበብዝህ ሕይወት ዓለም አቀፍ ስምምነት ፅ/ቤት በመገኘት የማህበረሰቦች እውቀት የሚጠበቅበትንና የሚበረታታበትን ብሎም ይህ እውቅት ለብዝሀ ሕይወት ሀብት መጠበቅ የሚውልበትን ሁኔታ ይወያያሉ። በተለይም በአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ሥራዓት ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ የማህበረሰቦች እውቀት ተገቢውን ቦታ የሚያገኝበትን ፣ በጄነቲክ ሀብት ዝውውርና አጠቃቀም ጊዜ የማህበረሰቦች ይሁንታ እንዲጠየቅ የሚመቻችበትን ብሎም ከብዝሀ ሕይውት ሀብት ጋር ተያያዥ ከሆነው ነባር እውቀት የሚገኘውን ጥቅም የእውቀቱ ባለቤት የሆኑት ማህበረሰቦች በአግባቡ የሚካፈሉበትን ሁኔታ ይነጋገራሉ።
ይህን ውይይት በማስመልከት የስምምነቱ ዋና ጸኃፊ ዶ/ር አህመድ ጆግላፍ እንደተናገሩት፤ “መጪውን ጊዜ ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ ነባር እውቀት በሰው ልጅ ላይ እየደረሰ ያለውን የከፋ አደጋ፣ ዘለቄታዊነት የሌለውን አጥቃቅምና በየጊዜው እየከፋ በመሄድ ላይ ያለውን እልቂት ጨምሮ፣ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና የሚጫዎትበትን የሥራ ፕሮግራም ጊዜ ሰጥተን እንወያያለን” ብለዋል።
ነባር ማህበረሰቦች ከብዝሀ ሕይወት ሀብት ጋር ተያያዥ የሆነ ነባር እውቀትና የአካባቢ እንክብካቤ ልምድ ለዘመናት አካብተዋል። ይህ እውቀትና ልምድ ለነባር ማህበረሰቦች ካለው ቀጥተኛ ጠቀሜታ ባሻገር ለሁሉም የሰው ልጆች የላቀ ዋጋ አለው።
እንደ ጽ/ቤቱ ገለፃ ውይይቱ የብዝሀ ሕይወት ዓመት (በዓል) መከበር ከሚጀምርበት ቀደም ብሎ መካሄዱ በነባር እውቀት ላይ የሚሠራው ቡድን በጉዳዩ የበለጠ ዝግጁ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር፤ በድህረ 2010 ነባር እውቀት ለብዝሀ ሕይወት ስምምነት 3ቱ ዓላማዎች መሳካት በሚያበረክተው አስተዋፅዖ የሰውን ልጅ ከአደጋ ለመታደግ የሚውልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ልዩ ዕድል ይፈጥርለታል።
ምንጭ፦ ብዝሀ ሕይወት ስምምነት ጽ/ቤት፤ ትርጉም፦ አብዮት ብርሃኑ
ማስታዎሻ፤ ብዝሀ ሕይወትን የተመለከቱ ጽሁፎችን/ዜናዎችን በድረ ገፃችን በአማርኛ ማተም የጀመርን መሆናችንን ስንገልጽ በደስታ ነው። እርሶም ጽሁፎችን/ዜናዎችን ቢልኩልን በደስታ እንቀበላለን።
Rate this article




